Rules and Policy
 

አዳዲስ ደንበኞችን ለመጠበቅ የተቀመጠ የስነምግባር መመሪያ

1. የተከለከሉ ተግባራት

የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ለአዳዲስ ደንበኞች የድርጅቱን ምርቶች ጠቀሜታቸው እና ከድርጅቱ ጋር አብሮ በመስራት ስለሚገኙ ጥቅሞች በሚገልፁበት ጊዜ አሳሳች፣ አታላይና ፍትሃዊ ያልሆኑ የሽያጭ ማስታወቂያዎችን ከመስጠት በሙሉ ይቆጠባል።

2. ግልጸኝነት

በገለፃ ወቅት ምንም እንኳን ደንበኛው ባይጠይቅም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያው በእውነት እና በግልፅነት ላይ ተመስርተው ስለ ራሳቸው አብረውት ስለሚሠሩት ድርጅት ስለምርቶቹ አይነት ፣ጥራት ፣አመራረትና አጠቃቀም ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።

3. ማብራሪያ አሠጣጥና የጥቅም ገለፃ

የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያዎች ለደንበኞቻቸው በትክክለኛው እና ለመረዳት በሚያስችል መልኩ የተሞላ የምርት ዓይነቶች ማብራሪያ የዋጋ ተመንና የኮሚሽን ክፍያን በዝርዝር ያስረዳሉ። በማስረዳት ሂደት ወስጥ በምርቶች አጠቃቀም የተገኘን የጤና እና የውበት ለውጥ እንዲሁም የተገኘን ከፍተኛ የገንዘብም ሆነ የአይነት ጥቅም በተመለከተ ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ወይንም መግለጽ የሚቻለው ተገኘ ስለተባለው ጥቅም ከድርጅቱ የተሰጠ የፅሁፍ ማረጋገጫ ሲኖር ብቻ ነው።

4. የማስታወቂያዎች ይዘት

ማንኛውም የፅሁፍ፣የምስል እና የድምፅ ማስታወቂያዎች ስለምርቶቹና ጥቅማቸዉ እንዲሁም ከድርጅቱ ስለሚገኙ ጥቅሞችና ክፍያዎች በፍጹም እውነተኝነት ላይ የተመሰረቱ ከአሳሳች አገላለጾች በጸዳ መልኩ ብቻ ይደረጋሉ፡፡ማንኛውም እንዲህ ያለ ማስታወቂያ / ገለጻ መስጠት የፈለገ የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ከማስታወቂያው ወይንም ከገለጻው ጋር የድርጅቱንና የራሱን ስም የድርጅቱን አድራሻ እና የራሱን ስልክ ቁጥር እንዲሁም ለምን ያህል ጊዜ ከድርጅቱ ጋር አብሮ እንደሰራ  እና ምን ያህል ሰዎች አብረውት በቡድን እየሰሩ መሆናችውን በግልጽ የማስቀመጥ ግዴታ አለበት፡፡

5 ምስክርነት

ማንኛውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ሰለምርቶች ጥቅምና ከሽያጭ ስለሚገኝ ጥቅም ለደንበኛው ገለፃ ሲሰጥ በቀጥተኛ ሽያጭ አሰራር ያልተፈቀዱ፣ያልተብራሩ፣የሚያሳስቱ ፣ጊዜ ያለፈባቸው፣ሊደረስባችው የማይቻል ማረጋገጫ ሊቀርብበት ከማይችል ምስክርነት መቆጠብ ይኖርባችዋል፡፡

6 ንጽጽሮችና ማንቋሸሾች

ማንኛውም የቀጥተኛ  ሽያጭ ባለሙያ ሊረጋገጡ ከሚችሉ እውነታዎች ውጭ አብረው የሚሰሩበትን ድርጅትም ይሁን የሌላ ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ አሰራርን የሚከተል ድርጅት መልካም ስም እና ዝናን ከሚያንቋሽሽ እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ የስም ማጠልሸት ከሚገልጹ የምርትና አገልግሎት የድርጅት ስምና አርማን ከሚያጎድፍ ንጽጽር ይታቀባሉ፡፡

7 ግላዊነትን ስለማክበር

በደንበኛው ግልጽ ፈቃድ እና ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ የደንበኛውን ግላዊ ህይወት በሚያውክ መልኩ በሚዛናዊ አእምሮ ልኬት ተገቢ ባልሆነ ሰአት ማወክ አይፈቀድም፡፡ እንዲሁም የቀጥታ ሽያጭ ባለሙያ የደንበኞቹን ግላዊ መረጃዎች ተገቢውን ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ያለደንበኛው ፈቃድና ፍላጎት ለሶስተኛ ወገን ምንም አይነት መረጃ አይሰጥም፡፡ 

8. ፍትሐዊነት

ማንኛውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ደንበኛው ስለቀጥተኛ ሽያጭ ያለውን የእውቀት ማነስ፣እድሜው ፣ሕመሙንና ፍላጎቶቹን በዘርፉ ያሉ የመግባቢያ ቋንቋዎች አለማወቁን በመጠቀም ደንበኛው በጫና ውስጥ ሆኖ ውሳኔ እንዲወስን ማስጨነቅ ፈፅሞ የተከለከለ ነው።

9. ሪፈራል ሽያጭ

ማናቸውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ደንበኛውን ምርት እንዲገዛና እንዲጠቀም ገለፃ ሲያደርግ፦

  1. ደንበኛው ምርቱን እንዲገዛ የሽያጭ ባለሙያው ገንዘብ እንደሚያበድረው መግለጽ
  2. ደንበኛው  ምርቱን ከገዛ በኋላ በእርግጠኝነት ሊታወቅና ሊደረስበት የማይችል ጊዜና ጥቅም ቃል በመግባት ሌሎች ሰዎች ብታመጣ መልሰህ ያወጣኸውን ገንዘብ ታገኛለህ በሚል የወደፊት ክስተቶች ላይ የተመሰረተ ቃል መግባት ፈፅሞ በጥብቅ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው

10. ገቢን ስለማሳወቅ

ማንኛውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ለአዳዲስ ደንበኞች ገቢ ስለሚያገኝባቸው ትክክለኛ መንገዶች ሲያስረዳ የገቢ መጠን እንደየአሰራሩ ከሠው ሠው እንደሚለያይ ለአንዱ የሰራው መንገድ ወይንም አንዱ ያገኘው ገቢ ሁሉም ሊያገኘው የማይችል መሆኑን ለስራው ተገቢ ትኩረትና እውቀት እንደሚጠይቅ ገቢ የሚገኘው በራሱ በደንበኛው እና በቡድን አጋሮቹ ጥንካሬ ብቻ መሆኑን በግልጽ ማስረዳት የሚጠበቅበት ሲሆን ማንኛውም የሽያጭ ሠራተኛ ያገኘውን ገቢ ሲያሳውቅ ያለውን የስራ ልምድ ለስራው የሠጠውን ጊዜና ትኩረት ለስራው የሚያወጣቸውን የጊዜ የገንዘብ እና የጉልበት ወጪዎች ጭምር መግለጽ ይጠበቅባቸዋል ።

11. የምርት ትዕዛዝና ጊዜ

ማንኛውም የቀጥታ ሽያጭ ባለሙያ ከደንበኛው ግልጽ ፈቃድ ውጪ እና የደንበኛውን አለማወቅ በመጠቀም ከሚያስፈልገው ምርት ውጭ እንዲገዛ ማስገደድ ወይንም ማታለል ፈፅሞ የተከለከለ ነው።

12. በቋሚ ደንበኝነት ስለመመዝገብ

ማንኛውም የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ ምርትና አገልግሎት ገዝቶ ከድርጅቱ ጋር መስራት የጀመረን ደንበኛ ወይንም ሌላ የሽያጭ ባለሙያ ስለምርቱና አሠራሩ ገለጻ የሠጠው አዲስ ደንበኛ መሆኑን እያወቁ ሆነ ብሎ ወይንም በከባድ ቸልተኝነት በማታለል እና በመደለል የሌላ ቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያን ደንበኛ የወሠደ ወይንም ቀደም ሲል የነበረውን የደንበኝነት ምዝገባ ትቶ ከእሱ ጋር እንዲሠራ የጠየቀ ያስገደደ ያሣሣተና የወሠደ እንደሆነ  ሽያጭ ባለሙያው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው ተደርጐ ደንበኛው መጀመሪያ ስለድርጅቱ ምርቶቹ ካስተዋወቀው የሽያጭ ባለሙያና ቡድን ጋር ብቻ እንዲሠራ ተደርጎ ሁለተኛ ምዝገባው ይሠረዛል።

13. ስልጠና እና ማማከር

ማንኛውም አዲስ ደንበኛ ወደ ድርጅቱ በጋበዘው እና ምርቶቹን ገዝቶ እንዲጠቀም ገለፃ ባደረገለት የቀጥተኛ ሽያጭ ባለሙያ የስልጠና እና የማማከር አገልግሎት የማግኘት መብት አለው።

14. የቡድን ገለፃ አሰጣጥ

ወደፊት ድርጅቱ በሚያወጣው የአሰራር ስርዐት መመሪያ እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀየር የሚችል መሆኑ ታሳቢ ሆኖ ማንኛውም በቁጥር ከ 10 ለበለጡ ለ አዲስ ደንበኛች በቡድን በአካልም ይሁን በበይነ መረብ (social media) የሚሰጥ ገለፃ በድርጅቱ እውቅና በተሰጣቸው ወይንም ልምድ ባላቸው የምርት አስተዋዋቂዎች ወይንም በሊድ ቲም ወይንም በአሶሺየይ ሊድ ቲም ወይንም ከነዚህ በአንዱ ገለፃ የመስጠት ብቃቱ በተረጋገጠለት ግለሰብ ብቻ ይሆናል።

15 በቀጥታ ውልን ስለሚያቋርጡ  ተግባራት

በዚህ ስር የተጠቀሱት ጥፋቶች እንደ ጥፋታቸው ክብደት ከማስጠንቀቂያ መስጠት አግዶ እስከማቆየት ብሎም ውልን እስከማቋረጥ የሚደርሱ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ የሚከተሉት ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ውል የሚያቋርጡ ተግባራት ይሆናሉ፡፡

15.1 ድርጅቱን ወይንም ደንበኞቹን ወይንም ከድርጅቱ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የስራ ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችንም ይሁን ድርጅቶችን የድርጅቱን ስምና አርማ በመጠቀም ያታለለ ያጭበረበረ እና የሰረቀ

15.2 በሀገሪቱ ባሉ ማንኛውም ፍ/ቤቶች በማንኛውም አይነት ወንጀል ተከሶ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈበት ግለሰብ

15.3 ከድርጅቱ አሰራር(System) ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ተግባራት ከሚሰሩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚሰራ ግለሰብ፡፡

15.4 በዚህ መመሪያ የተጠቀሰው ደንቦችን ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ለመማር ፍቃደኛ ያልሆነ፡፡

ምንም ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልገው ውሉ ይቋረጣል

16. የገንዘብ መቀጮ

ይህን ደንብ እና መመሪያ እንዲሁም የምርት አስተዋዋቂዎች ከድርጅቱ ጋር ያላቸውን የውል ስምምነት በመጣስ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅም ማንኛውም ግለሰብ ውሉን ማገድ እና ውሉን ማቋረጥ እርምጃ እንደተጠበቀ ሁኖ እንደጥፋቱ ክብደት ድርጅቱ ያመነበትን ከ ሁለት እስከ ሶስት  ወር የሚደርስ የኮሚሽን ክፍያ ወደ ድርጅቱ ተመላሽ እንዲሆን ያደርጋል።

17.መመሪያውን ስለማሻሻል እና ስለመለወጥ

ይህ መመሪያ እንደአስፈላጊነቱ ለስራው አመቺነት እና አፈፃፀም በድርጅቱ ሊለወጥ ወይንም ሊሻሻል ይችላል። ሆኖም ማንኛውም ማሻሻያ ሲደረግ አመቺ በሆነ መንገድ ለ ምርት አስተዋዋቂዎች እንዲያውቁት ይደረጋል።

2023 © Etcareproduct.com